ሸማቾች እና መብቶቻቸው

ሸማች ማን  ነው?

ሸማች የሚለውን ቃል የተለያዩ ሀገራት እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ እና ፖሊሲ የተለያየ ትርጉም ሰጥተዉት ይገኛል፡፡ እ.አ.አ. በ2016 የተሻሻለውን የተባበሩት መንግስታት የሸማቾች ጥበቃ መመሪያ (United Nations Guidelines For Consumer Protection) ሸማች ማለት በዋነኛነት ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ (household) ፍጆታ ግብይት የሚፈጽም የተፈጥሮ ሰው ነው በማለት የተረጎመው ሲሆን የUN አባላት ሀገራት የራሳቸውን ትርጓሜ ሊሰጡት እንደሚችሉ ይገልጻል። በሌላ በኩልበBlack’s Law Dictionary የተሰጠውን ትርጉም ብንመለከት ሸማች ማለት እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ለራሱ ጥቅም ወይም ለቤተሠብ አገልግሎት የሚገዛና ምንም አይነት መልሶ የመሸጥ ሐሳብ የሌለው የተፈጥሮ ሠው ሲሆን እቃዎችን የሚጠቀመው ለግል ፍጆታው ብቻና ለንግድ ተግባራት የማያውል ሠው ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የሀገራችን ህግም ከዚህ ጋር በተቀራረበ መልኩ ትርጉም ተሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅቁጥር 813/2006 አንቀጽ 2(4) ላይ፥ “ሸማች ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሠው የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሠው ነው” በማለት ተርጉሞታል፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው እንደ ሸማች ለመቆጠር ወይም በህግ ለሸማቾች የተሰጡትን ለዩ መብቶች ለመጠቀም የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፥

  1. ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ጥቅም ላይ የሚውል የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት መግዛት አለበት።
  2. የንግድ ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የገዛው በራሱ ገንዘብ ወይም ሌላ ሰው ከፍሎለት ሊሆን ይችላል። በሌላ አገላለጽ የዕቃው ወይም አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆኑ እንጂ ገንዘቡን ማን ከፈለ የሚለው ወሳኝ አይደለም ማለት ነው።
  3. የተገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት የመጨረሻው ተጠቃሚ መሆን አለበት። ይህም ማለት ሰውየው ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የገዛው መልሶ ሊሸጠው ወይም ሊለውጠው ወይም ሌላ ምርት ለማምረት በግብዓትነት ሊጠቀመው አስቦ ከሆነ ሸማች አይባልም ማለት ነው። 
  4. የተፈጥሮ ሰው መሆን አለበት። ይህም ማለት በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች ወይም ማህበራት (Legal Persons) ምንም እንኳን ለራሳቸው ጥቅም ላይ የሚያውሉትን ወይም መልሰው የማይሸጡትን ዕቃ ወይም አገልግሎት ቢገዙም እንደ ሸማች አይቆጠሩም ማለት ነው።

ይህ የሸማች ትርጓሜ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል። ለምሳሌ የህግ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች ለራሳቸው ፍጆታ በገዙት ዕቃ ወይም አገልግሎት ጉዳት ቢደርስባቸው ወይም ቢጭበረበሩ ምን መፍትሄ ያገኛሉ ወይም ለምን ጥበቃ አይደረግላቸውም የሚለው አንዱ ነው። ሌላው ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ አንድ ሰው ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ሳይሆን ለጓደኛው ወይም ለሌላ ለሚያውቀው ሰው ዕቃ ቢገዛ ለምን እንደ ሸማች አይቆጠርም፣ ያ ዕቃ ጉድለት ቢኖርበት ሰውየው ሊከስር ነው ወይ? የሚለው ነው። የመጀመሪያውን ጥያቄ በተመለከተ ድርጅቶች ሸማቾች አይደሉም ማለት ለሚፈጽሙት ግብይት ምንም አይነት የህግ ከለላ አይደረግላቸውም ማለት ሳይሆን መብታቸውን የሚያስከብሩት መደበኛዎቹ ንግድን፣ ግብይትን (ሽያጭን)፣ ውልን እና ተመሳሳይ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ህግጋትን በመጠቀም በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ነው ማለት ነው። በተጨማሪም ድርጅቶች ከተፈጥሮ ሰዎች (ግለሰቦች) የተሻለ የገንዘብም ሆነ የመደራደር አቅም ስላላቸው ጠበቃ በመቅጠርም ሆነ በራሳቸው በመሟገት መብታቸውን ማስከበር ይችላሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ሸማቾች ግን ግለሰቦች በመሆናቸው በእውቀትም ወይም በገንዘብ አቅም ወይም በሌላ ምክንያት ከነጋዴዎች ጋር በመደራደር ወይም በመሟገት መብታቸውን የሚያስከብሩት ሁኔታ ጠባብ በመሆኑ የተለየ የህግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዚህም ህግ መሰረት ጉዳያቸው ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጪ ፈጣን ውሳኔ ሊያገኙ በሚችሉበት ልዩ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይታያል ማለት ነው።    

የሸማች መብቶች

ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሸማች በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መሰረት የሚከተሉት መብቶች አሉት፡-

  1. የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግ ሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት ካሣ እንዲከፍሉት የመጠየቅ፣

ይህ መብት አንድ ሸማች የፈለገዉን ዕቃ ወይም አገለግሎት ከገዛና ከተጠቀመ በኋላ ወይም ግብይቱ ተፈፅሞ ሸማቹ በምርቱ ወይም በአገልግሎቱ ከተጠቀመበት በኋላ ስላሉት መብቶች ወይም የመፍትሄ አቅጣጫዎች የሚጠቁም መብት ነው፡፡ማንኛዉም ሸማች የሚገዛዉን የነግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚፈለግና ይህንንም ለማረጋገጥ የተለያዩ የመንግስት አካላት ተቋቁመዋል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ አንድ ምርት ወይም አገልግሎት ሸማቹን ህብረተሰብ ጤንነትና ደህንነት አደጋ ላይ ሲጥል መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ መብት የንግዱ ማህበረሰብ ከሸማቹ ጋር ያደረገዉን ግብይት ከጨረሰ በኋላ በተሸጠው ምርት ወይም አገልግሎት ዙሪያ ሊደርስ የሚችለዉን ጉዳት አያገባኝም ወይም አይመለከተኝም እንዳይል የሚያደርግና የሸማቹን ህብረተሰብ ጤንነትና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ጉልህ ድርሻ ያለዉ መብት ነው፡፡

ከነዚህ መብቶች በተጨማሪም ለሸማቹ የበለጠ የሚጠቅሙ ዋስትናዎች ወይም የህግ ወይም የውል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው የተሸጠለት ዕቃ ወይም አገልግሎት ጉድለት ያለበት ከሆነ፡

         ሀ)  የንግድ ዕቃው እንዲለወጥለት ወይም ዋጋው እንዲመለስለት፤ ወይም

         ለ) አገልግሎቱ በድጋሜ ያለክፍያ እንዲሰጠው ወይም የአገልግሎት ክፍያው እንዲመለስለት፤

ግዥው በተፈጸመ በ15 ቀናት ውስጥ ሻጩን የመጠየቅ መብት ያለው ሲሆን ሸማቹ ጉድለት ያለበትን ዕቃ ወይም አገልግሎት በመጠቀሙ ወይም ከላይ በተገለፀው መሠረት ሻጩ የቀረበለትን ጥያቄ ባለሟሟላቱ ለደረሰበት ማንኛውም ጉዳት ካሣ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት አለው፡፡

2. ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና አይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት፤

ይህ መብት እያንዳንዱ ሸማች ስለሚገዛዉ ዕቃና አገልግሎት ጥራትና ዓይነት ማለትም ሸማቹ ህብረተሰብ የሚገዛዉ እቃ ወይም አገልግሎት  የተሰራዉ ከምንድን ነዉ? ምን ምን ንጥረ ነገሮችን ወይም ዉህዶችን አካቶ ይዟል? የሚሉትን መረጃዎች በበቂና በትክክል እንዲያውቅ የሚያስችለዉ ሲሆን ይህም ሸማቹ ህብረተሰብ ዕቃ ወይም አልግሎት በሚገዛበት ወቅት ከራሱና ከቤተሰቡ ጤናና ደህንነት ጋር ተስማሚ የሆኑ ምርትና አገልግሎቶችን በቀላሉ ለይቶ እንዲገዛ የሚረዳዉ ነው፡፡

3. ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት

ይህ መብት አንድ ሸማች ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሚገዛበት ወቅት ለራሱ በሚስማማዉ መልኩ ከዋጋ፣ ከጥራት፣ ምርቱ ከተመረተበት ሃገር፣ አገልግሎት ዘመኑ ከሚያበቃበት እና ከመሳሰሉት አንፃር የማማረጥ መብት ወይም ነፃነት ያለዉ መሆኑን የሚያመላክት ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ መብት ለሸማቹ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ብቻ እንዲገዛ ጫና እንዳይደረግበትና በገበያዉ ዉስጥም እነዚህን የሸማቹን ፍላጎት የሚያሟሉ ምርቶችና አገልግሎቶች በስፋት እንዲኖሩ በር የሚከፍት ይሆናል፡፡

4. የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ፣

ይህ መብት ሸማቹ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች በመሄድ የሚፈልገውን ምርት ለመግዛት ወይም አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልግ የተለያዩ የገበያ ማዕከሎችንና የግለሰብ ነጋዴዎችን ሱቆች ወይም አገልግሎት መስጫ ተቋማት በመግባት ከዋጋ፣ ከጥራት፣ ከአይነትና ከመሰል ነገሮች አንፃር ድርድር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሸማቹ ህብረተሰብ ይህን ድርድር በማድረጉ ምክንያት ድርድር ያደረገበትን ምርት ወይም አገልግሎት እንዲገዛ በተለያየ መንገድ ጫና ሊደረግበትና ሊገደድ የማይችል መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

5. በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ እንዲሁም በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ፣

ይህ መብት በተግባር እንደሚስተዋለዉ የንግዱ ማህበረሰብ ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ንግድ ቦታዎች የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶቾን ፈልገው በሚሄዱበት ወቅት የተያዩ የማንቋሸሽ፣ የስድብ፣ የዛቻና ብሎም ለዱላ እስከመጋበዝና እስከመማታት የሚደርስ ተግባር የሚፈፀም መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ መብት የንግዱ ማህበረሰብ “ደንበኛ ንጉስ ነዉ” ብሎ እንዲያምን፣ እንዲያስብና በተግባርም እንዲገልፅ የሚያደርግ መብት ነዉ፡፡አንድ ሸማች የተወሰነ አገልግሎት ፈልጎ ወደ አንድ ነጋዴ ሱቅ ወይም ወደ አገልግሎት መስጫ ተቋም በሚመጣበት ወቅት ሸማቹ ከዚህ ቦታ ፍላጎቱን ሊያሟላ እንደሚመጣ ሁሉ ነጋዴዉም በዚህ ሸማች አማካኝነት ፍላጎቱ የሆነዉን ገንዘብ (ትርፍ) ሊያስገኝለት እንደሚመጣም ጭምር የሚያሳስብ መብት ነው፡፡

የሸማቾች ጥበቃ አስፈላጊነት እና የሸማቾች ጥበቃ ህግ በኢትዮጵያ

በአጠቃላይ የሸማቾችን መብት መጠበቅ ያስፈለገበት መሰረታዊ የሚባሉ ሁለት ምክንያቶቸ አሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ማህበራዊ ምክንያት ነው፡፡

  • ኢኮኖሚያዊ ምክንያት፡-

ይህ ምክንያት መነሻ የሚያደርገው በሸማቹና በነጋዴው መካከል ያለውን የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ነው፡፡ በንጽጽር ሲመዘን ሸማቾች ከነጋዴዎች ያነሰ የመደራደር አቅም ስላላቸው  የሚያደርጉት ግብይትም ሁል ጊዜ እኩል አይሆንም፡፡ ፍትህ የማግኘት አድማስ ብንወስድ ለአብነት የክርክር ወጭዎች መበራከት ግለሰቦች/ሸማቾች/ መብታቸውን በአግባቡ እንዳያስከብሩ የሚያደርጉ ምክንያት ናቸው፡፡[1]መረጃና እውቀትንም በተመለከተም በሁለቱ ተዋንያን መካከል ሰፊ ልዩነት በመኖሩ ምክንያት የገበያ ጉድለት ይከሰታል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ይህን የመከላከልና ጉድለቱን የሚያስተካክል የሸማቾች ጥበቃ ህግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት መንግስት የዜጎችን ደህንነትና መብት ለመጠበቅ ይገደዳል፡፡

  • ማህበራዊ ምክንያት

በአንፃራዊነት ሸማቾች ስለሚያደርጉት ግብይት ያላቸው እውቀት፣ የትምህርት ደረጃ የመደራደር አቅም በተግባር ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ሊደርስባቸው የሚችለው ጉዳት መገመት አያዳግትም በመሆኑም መንግስታት ለዜጐቻቸው ጥበቃ ማድረግ የመጀመሪያው ትልቅ ቦታ የሚሠጠው ከመሆኑ አንፃር የሸማቾችን መብቶች የሚያስከብር ስርዓት መዘርጋት እና ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲሠፍን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ አጠቃላይ የህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ህግ (Public law) ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሸማቾች ጥበቃ የሚደረግላቸው ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን እና አጠቃላይ የማህበረሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ነው፡፡

የሸማቾች ጥበቃ አስፈላጊነትን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ብንመለከተው ነጋዴዎች ትርፋቸውን፣ ሽያጫቸውን እና የገበያ ድርሻውን ለማሳደግ እና ሌሎች የንግድ አላማዎቻቸውን ለማሳካት ሲሉ በርካታ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ተግባራትን ይፈፅማሉ፡፡ ሚዛን መጭበርበር፣ ሀሰተኛ ማስታወቂያ ማስነገር፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ የንግድ ዕቃ ወይም መድሀኒት መሸጥ፣ ጉድለት ያለበትን የንግድ ዕቃ መሸጥ፣ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀሉ የንግድ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማቅረብ፣የጥራት ደረጃቸው የወረደ ምርቶችን መሸጥ በተደጋጋሚ ከሚፈፀሙ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ተግባራቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት በሚፈፀሙበት ጊዜ ሸማቹ ህብረተሰብ ለከፈለው ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ የንግድ ዕቃ እንዳያገኝ ከማድረግ ባሻገር ጤንነቱን እና ደህንነቱን አደጋ ላይ በመጣል ላልተገባ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ወጪ የሚዳርጉት ተግባራት ናቸው፡፡ ስለሆነም በእነዚህ እና ሌሎች መሰል ተግባራት ምክንያት የሸማቾች ጥበቃ አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የሸማቾች መብት ጥበቃ በኢትዮጵያ

በኢትየጵያ በተራጀ መልኩ የሸማቾች መብት ጥበቃ የተጀመረዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት የወጡ  የሸማቾችን እና የነጋዴዎችን ግንኙነት የሚያስተዳድሩ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ግን ነበሩ፡፡ እነዚህ ህጎች የሸማቹን መብት በተለየ ሁኔታ ዓላማ በማድረግ የተደራጁ ሳይሆን አጠቃላይ በንግድ ሥርዓቱ ዉስጥ ያለዉን ግንኙነት የሚያስተዳድሩ ናቸዉ፡፡ እነሱም፡-

  • የዉል ህግ፡- ይህ የህግ ዓይነት በተዋዋይ ወገኖች የመወዋል ነጻነት (freedom of contract) የሚሰጥና ሸማቾች በነፃ ፈቃዳቸዉ ያልሸመቱትን ዕቃ ወይም አገልግሎት እንዲወስዱ ወይም እንዲረከቡ አይገደዱም፡፡ይህም የሸማቾችን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ማለትም ሸማቾች የፈለጉትን ዕቃ ወይም አገልግሎት አማርጦ የመግዛት መብት የሚያጎናጽፍ መርህ የዉል ህግ ይዟል፡፡ በሌላ በኩል ግን  በውል ህግ መሰረትም የማጭበርበር፣ማስፈራራትና የማታለል የተደረገ ዉል ለሸማቾች ውል ለማፍረስ ምክንያት ይሆናል፡፡ እንደውሉ እንዲፈፀምና ጉዳት የደረሰበት አካል ካሳ ጥያቄ የማቅረብ መብትን ያጎናጽፋል፡፡ በተለይ በግዥ የተረከቡትን ዕቃ ጉድለት ካለበት የውል ህግ ዋስትና (warranty) በመስጠት ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ ስለሆነም የውል ህግ  የሸማቾችን መብት ከሚያስጠብቁ አንዱ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
  • ከዉል ዉጭ ሀላፊነት ህግ፡- ሸማቹ ዕቃዎችን ሲጠቀም ለሚደረስበት ጉዳት አምራቹን ሀላፊ በማድረግ የሸማቹን መብት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በዚህም የተገዙ ዕቃዎች በገዥዎች (ሸማቾች) ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ልክ ኃላፊነት (product liability) ማስቀመጥ የዳበረ አሠራር እንደሆነ በድንጋጌው  ላይ ተመላክቷል፡፡ በዚህ ህግ መሰረት የእቃዎች አቅራቢ ተጠያቂነት በሁለት መንገድ ይመሰረታል፤ በጥፋት ወይም ጥፋት ሳይኖር ሀላፊነት አለበት፡፡ የዕቃዎች አቅራቢ በጥፋት ላይ የተመሰረተ ሀላፊነት በምርት ሂደት ዉስጥ ጥንቃቄ ባለማድረጉ የሚመጣበት ሀላፊነት ሲሆን በሌላ በኩል ጥፋት ባይኖርበትም እቃዉን በማቅረቡ ብቻ በሸማቾች  ላይ ጉዳት ሲደርስ ካሳ የመክፈል ሀላፊነት አለበት (የፍትሃብሔር ህግ አንቀጽ 2028፣ 2085) ይመለከታል፡፡
  • የንግድ ህግ፡- የንግድ ህግ ስለንግድ አሰራርና ተገቢ ያልሆ አሰራር በማስቀመጥ አጠቃላይ ስለ ንግድ ስራ መርሆችን ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም ይህ ህግ ንግድን ያሳልጣል ብሎም  አቅርቦትንና ፍላጎትን በመምራት ሸማቹን በጥራት፣በመጠንና በዋጋ ተጠቃሚ በማድረግ የሸማቹን መብትና ጥቅም ያስከብራል፡፡
  • የወንጀል ህግ፡-  እንደሚታወቀዉ የወንጀል ህግ ዓላማ የማህበረሰቡን ደህንነት ከወንጀል አድራጊዎች መጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም የሸማቾችን ጥቅምና ደህንነት ዓላማ ይይዛል፡፡ በተለይም የሸማቹን ጤናና ደህንነት የሚያውኩ የተበረዙ የተቀላቀሉ ምርቶች፣ ምግቦችና መድሐኒቶች እንዳይቀርቡ በመከላከል የሸማቾች መብትና ደህንነት የማስጠበቅ ዓላማ አለዉ (የወንጀል ህግ አንቀጽ  525፣ 527፣ 537፣ 567፣) ይመለከታል፡፡ በተጨማሪም የንግድ አሰራሩን ጤናማነት ለመጠበቅ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ዉድድር በሚያደርጉ ላይ ቅጣት በማስተላለፍ የንግድ ስርዓቱንና የሸማቾችን ጥቅም ያስከብራል፡፡
  • የ1987 ዓ.ም የኢ.ፊ.ድ.ሪ ህገ-መንግስት፡-u›”kê- 41 e` ¾²?Ô‹” Ö?”’ƒ ¾SÖup ÓÈታ በመንግስት ላይ ተጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 1/3ኛዉ የህገ መንግስቱ ክፍል የሰብዓዊና ዲሞክረሲያዊ መብቶችን ትኩረት በመስጠት አመለክቷል፡፡ስለዚህ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የሚረጋገጠዉ የዜጎች ጤና፣ደህንነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ የዜጎች ማህበራዊ፣ፍትሃዊና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የመንግስት አቅም በፈቀደ መልኩ የማሟላት ግዴታ እንዳለበት በአንቀጽ(9) እና(13)ሃገሪቷ የተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ መንግስት ይህን ግዴታውን ለመወጣት የተለያዩ እርምጃዎች ይወስዳል፡፡ አንደኛው የገበያ ስርዓቱን በማስተካከልና የሸማቾችን መብትና ጥቅም በማረጋገጥ ይሆናል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ሀገራት ለምሳሌ ኬንያ የሸማቾችን ጉዳይ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በማስቀመጥ ያስከብራሉ (Article 46 of the Constitution of Kenya, 2010. These rights include: rights to goods and services of reasonable quality, information necessary for them to gain full benefits from goods and services, protection of their health, safety and economic interests and compensation for loss or injury arising from defects in goods and services).
  • የ ኮሜሳ (COMESA Dec, 2004) የንግድ ውድድር ህግ

ይህ ህግ አራቱ የፀረ-ውድድር ተግባራትን የሚደነግግ ሲሆን ይህንንም ህግ ሃገራችን ኢትዮጵያ መስራችና ፈራሚ ሃገር እንደመሆኗ መጠንና ይህም ህግ የሃገሪቱ የህግ አካል የሆነ ሲሆን (የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 9) ፀረ-ውድድር ተግባራትን በመቆጣጠርና ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን በማድረግ የሸማቹን ጥቅም ከማስከበር አንፃር የራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በተለይም ህጉ ስለ ፀረ-ውድድር ቁጥጥር ለማድረግ ዝርዝር ህግጋትን የያዘ ስለሆነ አሁን በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 813/2006 ያሉበትን ክፍተት በመሙላት ረገድ ሊጠቀስ የሚገባው ክፍለ አህጉራዊ ህግ ነው፡፡

  • አዋጅ ቁጥር 329/1995፡- የንግድ አሰራር አዋጅ ስለ ሸማቾች በቀጥታ ያስቀመጠው ጥበቃ አልነበረውም፡፡ይሁንና ቀጥተኛ ባይሆንም የንግድ አሰራርን መቆጣጠር በራሱ የሸማቾችን መብት በከፊል መጠበቅ ሊሆን ይችላል፡፡ የገበያ ስርዓቱን ጤናማነት ማረጋገጥ ማለት ውድድር ይሰፍናል በዚህ የገበያ ስርዓት ነጋዴዉ የሚደራደረዉ ጥራት ያለዉ ምርት በማቅረብ፣የዕቃዉን መጠን በመጨመርና የዕቃዉን ዋጋ በመቀነስ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለሸማቹ ጥቅም አይነተኛ ኢኮኖሚዊ መፍትሄ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በዚህ አዋጅ መሰረት የሸማቾች መብት ማስጠበቅ ይቻላል፡፡ ይሁንና የገበያ አሰራር ጤናማ መሆን ብቻዉን የሸማቾችን መብትና ጥቅም አያስጠብቅም ስለሆነም በኢትየጵያ ራሱን የቻለና ወጥ የሆነ ህግ አስፈልጓታል ማለት ነዉ፡፡ 

ይህን አዋጅ በመተካት 685/2002 የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ በማስከተለም አዋጅ ቁጥር 813/2006 በኢትዩጵያ ውስጥ መሠረታዊ የሸማቾችን ማህበራዊ ፍትህ፣የሸማቾችን ጤንነትና ተመጣጣኝ ዋጋ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች እንዲያገኙ አጠቃላይ ደህንነት ለማረጋገጥ ዓላማ በማደረግ ታዉጇል፡፡


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *